logo

notes

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በቅርቡ በቴክኖሎጂ በመታገዘ የከፍተኛ ትምህርትን ለማስቀጠል መወሰኑን መግለፁ ይታወቃል፡፡ ይሄንንም ተከትሎ በትግበራው ዙርያ ከስጋትና ከመረጃ ጉድለት የተለያዩ ጥያቄዎች ተነስተዋል፡፡ አፈፃፀሙ ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ መስጠት አስፈላጊ ሆኖ ስለተገኘ ይህ ፅሁፍ ተዘጋጅቷል፡፡ የተነሱት ጥያቄዎች ጠቅለል ተደርገው ሲታዩ የቅድመ ምረቃ ተማሪዎችን የተመለከቱ፣ የኢንተርኔት ዋጋ ውድ መሆን ፣ የኔትወርክ ችግር መኖርን፣ የመብራት አለመኖርና መቆራረጥን፣ ሁሉም ተማሪዎች ተመጣጣኝ የኢኮኖሚ አቅም ሳይኖራቸው ትግበራው የሚያስከትለውን ኢ-ፍትሃዊነትና ቢተገበር ውጤታማ ላይሆን ይችላል ከሚል ስጋት የሚነሱ ናቸው፡፡ ዓለማችን በተለያዩ ጊዜያት የሰው ልጆችን ህልውና በሚፈታተኑ አስቸጋሪ ወረርሽኞች ውስጥ አልፋለች፡፡ ከነዚህም አንዱ በዘመናችን ያጋጠመን ኮቪድ 19 ነው፡፡ ቫይረሱ በጣም በአጭር ጊዜ በመላው ዓለም መዛመት ከመቻሉ ጋር ተያይዞ የበርካታ አገራትን ዜጎች ከቤት ውጭ ከሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ገድቧል፡፡ በሁሉም ዘርፎች ዓለምን ለቀውስ ዳርጓል፡፡ ታዲያ ይህ ቫይረስ ወደ አገራችን መግባቱን ተከትሎ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት እና የዜጎችን ህይወት ለመታደግ ሲል መንግስት የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡ ከነዚህም አንዱ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎችን ወደየቤተሰቦቻቸው መመለስ ነው፡፡ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ቫይረሱ መቼ በቁጥጥር ስር ውሎ እነዚህ ተማሪዎች ወደቀድሞ እንቅስቃሴያቸው እንደሚመለሱ ስለማይታወቅ ትምህርትን ከማስቀጠል አንፃር የተለያዩ አማራጮችን መመልከት አስፈልጓል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎችን ስንመለከት በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በቀውስና አደጋ ጊዜ ስለትምህርት ማስቀጠል “Education Response in Crises and Emergencies” ሲያስረዳ በችግር ጊዜ ትምህርት ሙሉ በሙሉ እንዳይቋረጥ አገራት የተለያዩ የትምህርት ማስቀጠያ መንገዶችን ተከትለው እንዲሰሩ ያስቀምጣል፡፡ በተለይም “Education 2030 Incheon Declaration and Framework for Action“ ላይ በተለያዩ የአደጋ ጊዜዎች በመደበኛም ሆነ ኢ-መደበኛ መንገዶችን በመጠቀም ተለዋጭ የመማር-ማስተማር ዘዴዎችን በመተግበር አካታችና ፍትኃዊ ትምህርትን ተደራሽ ማድረግ እንዳለባቸው ያስቀምጣል፡፡ ስለሆነም ይህ በትምህርት ላይ የነበሩና በዚህ ወረርሽኝ ምክንያት ትምህርታቸውን ያቋረጡ ተማሪዎቻችንን በተቻለ መጠን በሚቻለው ሁሉም አማራጭ ንባቦችን እንዲያገኙ በማድረግ እያነበቡ እንዲቆዩና ከትምህርታቸውም እንዳይቆራረጡ ማድረግን ግብ አድርጎ እየተሰራ ያለ ተግባር ነው፡፡ ስለዚህ እንደአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ባለን አቅም፣ ሀብትና ግብዓት የከፍተኛ ትምህርቱን በቴክኖሎጂ በመታገዝ ማስቀጠሉ ጊዜ የማይሰጠው ተግባር በመሆኑ ውሳኔው ተላልፏል፡፡ በዚህም #የቅድመ_ምረቃ ተማሪዎችን በተመለከተ የሁለተኛ ሴሚስተር የሁሉም ትምህርት አይነቶች ሞጁሎች፣ አጋዥ ንባቦች እና ሌሎችም በየትምህርት አይነቱ ተሰንደው የሚገኙባቸው ቄብሳይቶችን የማሟላት ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ፡፡ በዚህም - የተዘጋጁ የኮርስ ማቴሪያሎችና አጋዥ የትምህርት መጽሃፍቶች ተደራሽ የሚሆኑበት የዲጂታል ላይብረሪ ዝግጁ ተደርጓል፡፡ (http://ndl.ethernet.edu.et/) አስፈላጊ በሆኑ የትምህርት ይዘቶች እየበለፀገ ይገኛል፡፡ - እንዲሁም በርካታ ይዘቶችን የያዘዉ የ TechIn ላይብረሪ ዝግጁ ሆኗል (http://library.techin.et/) - የኦንላይን ትምህርት መስጠት የሚያስችል የLearning Management System/MOOCS ዝግጁ ተደርጓል፡፡ (https://courses.ethernet.edu.et/) እንዲሁም ተማሪዎች ምንም አይነት የገቢ ምንጭ የሌላቸው መሆኑን ከግምት ውስጥ በማስገባት በስልክም ይሁን በላፕቶፕ እንዲሁም በታብሌት ወደእነዚህ ዌብሳይቶች ገብተው በሚያነቡበት ጊዜ ከክፍያ ነፃ እንዲሆን ለማድረግ ከኢትዮ ቴሎኮም ጋር ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ፡፡ እንደተገለፀው ወረርሽኙ መቼ እንደሚገታ አይታወቅም፡፡ ነገር ግን ወረርሽኙ ስጋት አለመሆኑ ተረጋግጦ ተማሪዎች ወደትምህርት ገበታቸው እስከሚመለሱ ድረስ በተለያዩ ዌብሳይቶች ለንባብ የቀረቡላቸውን ማቴሪያሎች እያነበቡ ይቆዩና ሲመለሱ እንደየተቋማቱ ተጨባጭ ሁኔታ ቀሪ ትምህርታቸውን የሚያጠናቅቁበት ፕሮግራም ይቀይሳሉ፡፡ የ #ምረቃና #ድህረ_ምረቃ ተማሪዎችን በሚመለከት አብዛኞቹ የማስተርና የፒኤችዲ ተማሪዎች ምርምር ላይ እንደመሆናቸው ሁሉም ዩኒቨርስቲዎች እንደራሳቸው ተጨባጭ ሁኔታ ሙሉ በሙሉ ትምህርቱን ኦንላይን ለማስቀጠል እንዲያመቻቹ ሆኗል፡፡ በዚህም ለመማር ማስተማሩ የሚያግዙ ማቴሪያሎች ኦንላይን፣ በኢሜይል እና ሌሎች ዘዴዎች ለተማሪዎች እንዲቀርቡ እየተሰራ ይገኛል፡፡ ምርምሮቻቸውን ያላጠናቀቁና ዳታ ለማሰባሰብ የግድ መውጣት ከሚያስፈልጋቸው ውጭ ያሉት በሙሉ የመመራቂያ ጽሁፋቸዉን የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን ተጠቅመው እንዲያቀርቡ ይመቻቻል፡፡ የድህረ ምረቃ ተማሪዎች ከአማካሪዎቻቸዉ ጋር የሚገናኙበት የኦንላይን የቪዲዮ ኮንፈረንስ ማድረግ፣ ማንኛዉንም ሰነዶችን ማጋራት ሌሎችንም የቨርቹዋል ግንኙነቶች ማድረግ የሚያስችል የO.365 Teams ቴክኖሊጂ ዝግጁ ተደርጓል፡፡ በተጨማሪም በሃገር ዉስጥ የተሰሩ የ Thesis and Dissertations ሰነዶች ለማጣቀሻ እንዲሆኑ በ (https://nadre.ethernet.edu.et/) ዝግጁ ሆነዋል፡፡ በተጨማሪም አብዛኞቹ የ Educational Private አገልግሎቶች ከኢተርኔት ዳታ ማዕከል የሚሰጡ ስለሆነ፣ ለዳታ ማዕከሉ ለጊዜዉ ያልተቆጠበ የኢንተርኔት ባንድዊድዝ ኢትዮ ቴሌኮም እንዲያቀርብ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በመነጋገር ላይ ይገኛል፡፡ ይህ አቅጣጫ እንዳለ ሆኖ ዩኒቨርስቲዎች እንደየትምህርት ክፍላቸውና የትምህርት አይነቶቹ እንደሚያስፈልጓቸው ተጨማሪ ሁኔታዎች እያዩ ሌሎች የመገናኛ ፕላትፎርሞችንም የሚያቻቹ ይሆናል፡፡ በመጨረሻም የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አሁን በዓለማችን ያጋጠመውን ፈተና ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ በሁሉም ዘርፍ ያለውን የአገራችንን እና የዜጎቿን ነባራዊ ሁኔታ ባገናዘበ መልኩ እና በተቻለ መጠን ሁሉ ትምህርትን ተደረሽ ለማድረግ እየሰራ እንደሆነ ለመግለፅ እንወዳለን፡፡ ይህ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ትክክለኛ የTelegram Channel ነው። ይቀላቀሉ! በሌላ ማራጭ ትክክለኛ መረጃ ያግኙ። https://t.me/MinistryoSHE

Image

Leave comment