Assosa University

የልዩ ፍላጎት ትምህርትን ውጤታማ ለማድረግ በትብብር መስራት እንደሚገባ ተገለፀ

(ጥረ 24/2017 ዓ/ም) አሶሳ ዩኒቨርሲቲ ከአሶሳ ከተማ አስተዳደር ትምህርት መምሪ ጋር በመተባበር የልዩ ፍላጎት ትምህርት አተገባበር ዙሪያ ለርዕሳነ መምህራን፣ ለሱፐርቫይዘሮች፣ ለመምህራን እና ለባለ ድርሻ አካላት የአቅም ግንባታ ስልጠና ሰጠ።
 
በሥልጠናዉ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የከተማ አስተዳደሩ ትምህርት መምሪ ኃላፊ ክብርት ወ/ሮ ጎጃም አያና ሲሆኑ ትምህርትና ስልጠና ለአካል ጉዳተኛ ተማሪዎች ተደራሽ ለማድረግ የልዩ ፍላጎት/አካቶ ትምህርት ስትራቴጂ ተቀርፆ ዜጎች በእኩልነት የትምህርት ፍትሀዊነት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል ፡፡
 
ወ/ሮ ጎጃም አያና አክለዉም የልዩ ፍላጎት ትምህርት በማሻሻል የትምህርት ተሳትፎን ለማሳደግ ጥራትና ተገቢነቱን የጠበቀ ፍትሐዊ የትምህርት አገልግሎት አሰጣጥ ዉጤታማ ለማድረግ ሁሉም ባለ ድርሻ አካላት በርብርብ እንዲሰሩ አሳስበዋል፡፡
 
በስልጠናዉ መልዕክት ያስተላለፉት የማህበረሰብ ጉድኝት ዳይሬክተር ዶ/ር ተፈራ ተሾመ ዩኒቨርሲቲዉ በክልሉ በትምህርት እና በተለያዩ ማህበራዊ ስራዎች ላይ የማህበረሰብ አገልግሎት ስራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ ጠቅሰዉ ትምህርት ለአንድ ሀገር ዕድገት ቁልፍ ሚና እንዳለዉ በመገንዘብ የትምህርት ጥራትን ለማምጣት እንደሀገር የተጀመሩ ለዉጦችን በመደገፍ ዩኒቨርሲቲዉ የድርሻዉን እየተወጣ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
 
በቀጣይም በክልሉ የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ተፈታኝ ተማሪዎችን የማለፍ ምጣኔ ለማሳደግ የዩኒቨርሲቲዉ ምሁራን ለመምህራንና ለትምህርት ዘርፍ አመራሮች በመማር ማስተማር ልምድ የማካፈል እና ይህንን መሰል ስልጠና መስጠት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
በስልጠናዉ የአሶሳ ከተማ ምክትል ከንቲባ ክቡር አቶ ንጋቱ ቂልጡ ተገኝተዉ መልዕክት አስተላልፈዋል።
 
በስልጠናዉ በአሶሳ ከተማ አስተዳደር ስር የሚገኙ ከመንግስት እና ከግል ት/ቤት የተዉጣጡ አንድ መቶ የሚሆኑ ርዕሳነ መምህራን፣ሱፐርቫይዘሮች፣ መምህራን እና ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡
 
ስልጠናዉ በምልክት ቋንቋ፣ የብሬል አፃፃፍ፣ የአካቶ ትምህርት አሰጣጥ እና የሞንቶሰሪ ኪት አጠቃቀም ዙሪያ ለ02 ቀናት ሲሰጥ ቆይቶ ዛሬ ተጠናቋል፡፡
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን
Twitter:Assosa University (@AssosaU) / X
Email: pir@asu.edu.et

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *